አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ-እስራኤል ፓርላማዊ ወዳጅነት ማኅበር በእስራኤል ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት እና ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የገቢ ማሠባሰቢያ መርሃ-ግብር ለማዘጋጀት እና አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት አግባብ ላይ መከሩ፡፡
የኢትዮጵያ-እስራኤል ፓርላማዊ ወዳጅነት ማኅበር ሊቀመንበር ጋዲ ይቫርካን ÷ የውይይቱ ዓላማ ኢትዮጵያ በእንዲህ ያለ ወቅት ስትሆን መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ ድጋፉን ለማሰባሰብ በሚቻሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር መሆኑን አስምረውበታል፡፡
በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ ÷ በኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ስለተፈጸመው ወረራ፣ አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል እና የመሠረተ-ልማት ውድመት አንስተዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱንም ጠቁመዋል፡፡
ማኅበሩ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ለማሰባሰብ በመምከሩም ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ በግጭቱ እና በድርቁ ጉዳት የደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አስቸኳይ የጤና ፣ የምግብ አቅርቦት እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያሻቸው ለይቶ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚቀርብ ተመላክቷል፡፡
በውይይቱ የእስራኤል ፓርላማ አባላት፣ የእስራኤል መንግስት ባለሥልጣናት፣ ባለሐብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡