አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ መዲናችን የህብረብሄራዊነታችን መገለጫ የአንድነታችን ማሳያ ነች” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ከፈተና ወደ ልዕልና በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለውን የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ አስመልክቶ ብልፅግና ፓርቲ ያዘጋጀው የእራት ፕሮግራም በወዳጅነት ፓርክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፥ አዲስ አበባ የብልፅግናን የመጀመርያ ጉባኤ ስታስተናግድ እንግዶች መጡ ሳይሆን ልጆቼ መጡ ብላ ነው የምትቀበለው ብለዋል፡፡
ምክንያቱም አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ መዲናችን የህብረብሄራዊነታችን መገለጫ የአንድነታችን ማሳያ ስለሆነች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አክለውም አዲስ አበባ የለውጣችን ፍሬዎች በምስክርነት ይዛ ብልፅግናችን አይቀሬ መሆኑን የምታረጋግጥ ከተማ ናትም ነው ያሉት፡፡
የወንድማማችነት ፓርክ ከስያሜው ጀምሮ የብልፅግናችንን እሳቤ በተግባር መሬት ላይ እያደረስን እንዲህ ዓይነት ጉባኤ ልናካሂድበት የምንችለው ቦታ ጭምር ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ የአብርሆት ቤተ መፃህፍት ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን መዲና መገለጫነት በሚያሳይ መልኩ መልሶ የታደሰው የማዘጋጃ ቤት ህንፃ፤ እንዲሁም የቸርቸር ጎዳና ተስፋችንን ያለመልማል፥ ብልፅግናችንንም ያፀናል በማለት ገልፀዋል፡፡
በዝግጅቱ ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ የጉባኤ ተሳታፊዎችና የክብር እንግዶች የታደሙ ሲሆን÷ የተለያዩ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልፁ ትዕይንቶች መቅረባቸውን ከአዲስ አበበ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡