የሀገር ውስጥ ዜና

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

By Feven Bishaw

March 13, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትረያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈጸመው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ፣ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት የሃማኖቶች ተቋማት መሪዎችና ምዕመናን በተገኙበት ነው።

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ዕርፍት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዕረፍት የተሰማቸውን ልባዊ ሐዘን ገልጸዋል።

“ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አምላካቸው ሄደዋል፤ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት ያሳርፍልን፤ በክብር እንሸኛቸው” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አስክሬን ሽኝት መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚያምኑትን አምላክ እና የሚወዷትን ቤተክርስቲያን በታማኝነት ያገለገሉ አባት መሆናቸውን ገልጸዋል።

“አባታችን ፈታኝ ነገር ሲገጥመን በጸሎት እና በምክር ያግዙኝ ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ “ከአባታችን ልንማር የሚገባን ኦርቶዶክስ ከነ ቀኖናዋ፣ ከነ ትውፊቷ እና ማንነቷ ወደ ትውልድ እንድትሸጋገር ከግጭት፥ እርስ በርስ ከመሰዳደብ ወጥተን በመተባበር መንፈስ አብረን መስራት እንዳለብን ነው” ሲሉም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ለአገራቸው በየደረጃው ከልጅነት እስከ እውቀት የሚገባቸውን ሁሉ አግልግሎት ማበርከታቸውን አውስተዋል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአስክሬን ሽኝት መርሀ ግብር ላይ የተገኙት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ባደረጉት ንግግር ÷የሰውን ልጅ መልካም ሥራና ምግባር እንደሚያስከብረው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መማር ይገባል ብለዋል።

ከብጹዕነታቸው የሰላምና ይቅርታን መንገድ በመማር ለአብሮነትና አንድነት ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ የኢትዮጵያ የተናገሩት ደግሞ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ ናቸው።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዕረፍት አስመልክተው ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት÷ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ታላቅ አባት እንደነበሩ አስታውሰው÷ አሁንም ወደ ፈጣሪያቸው ሄደው ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ይጸልያሉ ብለዋል።

ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ 4ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም. ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንበራቸው ላይ የቆዩት ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር።

ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ከጥቂት ወራት በኋላ ከወቅቱ መንግሥት ባጋጠማቸው ፖለቲካዊ ጫና መንበራቸውን ለቀው ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ከአገር ወጥተው ለ26 ዓመታት በአሜሪካ በስደት መቆየታቸው ይታወሳል።

ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባደረጉት የዕርቅ ጥረት “ ከልጄ ጋር አገሬ እገባለሁ “ ብለው ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ84 ዓመታቸው የካቲት 24 ቀን 2014 ዓመተ ምህረት ምሽት ነበር ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!