የሀገር ውስጥ ዜና

በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም የስርቆት ወንጀል እየተባባሰ መምጣቱ ተገለፀ

By Meseret Awoke

March 15, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለቀላል ባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢልቱማ ቂጣታ ገልፀዋል፡፡

አቶ ቢልቱማ እንዳሉት ፥ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል የሃገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲስተጓጎል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ብቻ በዚሁ የቀላል ባቡር በተዘረጋው የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ ከ2 ሚሊየን 197 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ርዝመቱ 1 ሺህ 363 ሜትር የኤሌክትሪክ ኬብል ስርቆት እንደተፈፀመ ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት እስካሁን ባሉት ወራት ደግሞ በገንዘብ 18 ሚሊየን 535 ሺህ 688 ብር የሚገመት ርዝመቱ 11 ሺህ 345 ሜትር ኬብል ስርቆት መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡

በዚህም በድምሩ 12 ሺህ 708 ሜትር የሚረዝም የኬብል ስርቆት ተፈፅሞ፤ በተቋሙ ላይ ከ20 ሚሊየን 733 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

አብዛኛው የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት እየተፈፀመ የሚገኘው በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ፣ በየካ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በለሚኩራ ክፍለ ከተሞች መሆኑን የገለፁት አቶ ቢልቱማ ፥ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን የራሳቸው ንብረት መሆኑን አውቀው ከመሰል እኩይ ተግባር ሊጠብቁት ይገባል ብለዋል፡፡

በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በሃገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669 መሰረት በከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሶ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት የሚቀጣ ሲሆን፥ እንደወንጀል ድርጊቱ እየተለየ በአማራጭ በኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 ዓ.ም የወንጀል ቅጣት ድንጋጌዎቹ መሰረት በመሰል ተግባራት ላይ ሲሳተፍ የተገኘ ወይም ተባባሪ የሆነ ማንኛውም አካል በእስራትና በገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።

በተጨማሪም በወንጀል ምክንያት የተገኘ መሆኑን እያወቀ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት በመግዛትም ሆነ በተውሶ፣ በስጦታ፣ በመያዣነት የተቀበለ ወይም በማናቸውም አኳኋን የወሰደ፣ የተገለገለ የደበቀ ወይም ያስቀመጠ፣ አሳልፎ የሸጠ፣ በሽያጭ ሂደት ወስጥ አገናኝ ሆኖ የተሳተፈ ማንኛውም ግለሰብ በሃገሪቱ ወንጀል ሕግ አንቀፅ 682 መሰረት ተከሶ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል።

በ2014 በጀት ዓመት በተደረገ የማጣራት ስራ በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ በቁጥር ከ18 በላይ ‘’የስርቆትና ጉዳት ማድረስ’’ የወንጀል ተግባራት ተፈፅመው ለተለያዩ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ምርመራ ተደርጎ ክስ እንዲመሰረት የሚጠይቁ ማመልከቻዎች መቅረባቸውና በዚህም ከዘጠኝ በላይ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!