የሀገር ውስጥ ዜና

በአራት የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች መካከል የአግሮ ኢንዱስትሪ የሥራ ፈጠራ ውድድር እየተካሄደ ነው

By Meseret Awoke

March 17, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃዋሳ፣ አዳማ፣ ደብረማርቆስ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የአግሮ ኢንዱስትሪ የሥራ ፈጠራ ውድድር እየተካሄደ ነው፡፡

በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የአዳዲስ ሥራ ዕድል ፈጠራና ፕሮጀክቶች ዳይሬክቶሬት እና የተለያዩ አጋር አካላት በትብብር በአራት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ሲያካሂዱት የቆየው ውድድር ዛሬ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሻለ ሥራ የሚፈጥር ሃሳብ እና ምርት ያቀረቡ አምስት ወጣቶችን በመለየት እንደሚጠናቀቅ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ወጣቶቹ በነበሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ መሆናቸውን የአውሮፓ ህብረት ተወካይ አቶ ቴሬሳ ጃለታ ተናግረዋል፡፡

ለወጣቶች እና ሴቶች በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በአውሮፓ ህብረትና ሌሎችም አካላት በተነደፈው ፕሮጀክት ሥራ ፈጣሪዎች የተሻለ መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ መቻሉንም ተወካዩ ገልጸዋል፡፡

የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ጂ አይ ዜድ ተወካይ የሆኑት ላሪስ ፊቼል በበኩላቸው፥ በየዓመቱ የሥራውን ዓለም የሚቀላቀሉ ወጣቶች ለአገሪቱ ብልፅግና ትልቅ ዕድል እንደሆኑ አንስተው፥ ከትምህርት ተቋማት ጋር መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ የዩኒቨርሲቲዎች ውድድር 17 ቡድኖች ዩኒቨርሲቲዎቻቸውን ወክለው ምርቶቻቸውን ይዘው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

የውድድሩ አስተባባባሪ የአይስ አዲስ መስራች አቶ ማርቆስ ለማ ፥ ችግሮችን እንደ ዕድል ተጠቅሞ ሥራ መፍጠር ተገቢ ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!