አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመመሪያ ጥሰት ፈጽመው በተገኙ ተጨማሪ ሁለት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱን የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አስታወቀ ።
ባለሥልጣኑ የደረሱትን የኅብረተሰብ ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ ባካሄደው ድንገተኛ ጉብኝት ተጨማሪ ሁለት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ካምፓሶች/ ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱ ተመላክቷል፡፡
በዚሁ መሰረትም ‘ሰቭን ስታር’ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ /ደብረ ብርሃን ካምፓስ/ እና ‘ራዳ ኮሌጅ’ /ደብረሲና ካምፓስ/ መሆናቸውን ከትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ራዳ ኮሌጅ ቀደም ሲል እውቅና ሳይኖረው እራሱን ራዳ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ የሚል የደረጃ ስያሜ ተጠቅሞ በመገኘቱ የማስተካከያ እርምት እርምጃ ተወስዶበት እንደነበረ የገለጸው ባለስልጣኑ÷ በተጨማሪ በተደረገ ምርመራ ከመመሪያ ውጭ በደብረሲና ከተማ ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይኖረው በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ ደረጃ ተማሪዎችን እየመዘገበ በመገኘቱ የእርምት እርምጃ ተወስዶበታል፡፡
በዚህም ራዳ ኮሌጅ በደብረሲና ከተማ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ እስከ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም እውቅና ፈቃድ እንዳይሰጠው ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡
በተመሳሳይ ሰቭን ስታር ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በደብረብርሃን ከተማ ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይኖረው በቅድመ ምረቃ ደረጃ ተማሪዎችን እየመዘገበ በመሆኑ÷ ኮሌጁ በደብረብርሃን ከተማ የከፈተውን ካምፓስ በመዝጋትና የመዘገባቸውን ተማሪዎች በማሰናበት ለባለስልጣኑ በ10 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ ተወስኗል፡፡
በተጨማሪም በደብረብርሃን ከተማ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ እስከ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም እውቅና ፈቃድ እንዳይሰጠው ባለስልጣኑ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!