የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ፍፁም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ህጎችን እንዲቃወሙ ጥሪ አቀረቡ

By Melaku Gedif

March 21, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ህጎችን እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አምባሳደሩ ጉዳዩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷በቅርቡ በአሜሪካ ሁለቱ  ምክር ቤቶች  ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 የሚባሉ ረቂቅ ህጎች ኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫናዎችን ለመፍጠር በውይይት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ረቂቅ ህጎቹ  በተለይም ኢትዮጵያ እራሷን የመከላከል ሉዓላዊ መብቷን ለማስጠበቅ እራሷን በጸጥታው ዘርፍ እንዳታደራጅ  የሚከለክሉ እንዲሁም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ  እንዳትጠናከር ለማድረግ ያለሙ መሆናቸውን  አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በጦርነቱ የወደሙ መሰረት ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ብድር እና እርዳታ እንዳይገኝ የሚከለክሉ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

ዜጎች በሀገር ቤት ውድ ህይወታቸውን ከፍለው ያረጋገጡትን ሉዓላዊነት ለማስከበር÷ በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን  በዓለም አቀፉ መድረክ  የሚመጡ ጫናዎችን በጋራ ሆነን መመከት አለብንም ብለዋል፡፡

ስለሆነም  በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ተትውልደ ኢትዮጵያውያን በግንባር የተሸነፉ አካላት በሌላ በኩል ይዘውት የመጡት ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199  የተሰኙ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ የተጠናከረ ተቃውሞ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡