አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ይዞታ በሌላቸው ግለሰቦች ስም ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ወስደዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ 3 ተከሳሾች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው ዛሬ ትእዛዙን የሰጠው።
ተጠርጣሪዎቹ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቦሌ አራብሳ አካባቢ ባለይዞታ ባልሆኑ ግለሰቦች ስም ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ወስደዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ነው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ የታዘዘው፡፡
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት የካሳ ይዞታ ማረጋገጥና ማጽደቅ ዘርፍ ሰራተኞች የነበሩ 21 ተከሳሾች ናቸው በድርጊቱ እንደተሳተፉ የተጠረጠሩት።
በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት በቦሌ አራብሳ አካባቢ በውሃና ፍሳሽ ተቋም ለሚሰራ ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ስራ ይዞታ ከሌላቸው ግለሰቦች ጋር በዘመድና በጥቅም በመተሳሰር የመሬት ይዞታ እንዳላቸው ተደርጎ ስም ዝርዝር መግባቱ ተጠቅሷል፡፡
ግለሰቦቹ በይዞታ ባለቤትነት በሀሰት የተመዘገቡ ቤተሰብና የተለያዩ ግለሰቦችን ውክልና በመውሰድ ይዞታ በማረጋገጥ፣ የይዞታ ካሳ በማጽደቅና ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ያልተገባ ካሳ ገንዘብ በመውሰድ ተከሰዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግም እንደተሳትፎ ደረጃቸው የካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም የከባድ ሙስና ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረበባቸውን ክስ ለማንበብና ያልቀረቡ ቀሪ 18 ተከሳሾች እንዲቀርቡ የሰጠውን ትዕዛዝ ውጤት ለመጠባበቅ ዛሬ ተሰይሞ ነበር።
ሆኖም የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ስራ አስፈጻሚ አቶ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ 18ቱ ተከሳሾች ችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ ያልቀረቡ 18 ተከሳሾችን ፖሊስ ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ÷ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት 14ኛ ተከሳሽ በቀለ ገረሱ፣ 15ኛ ተከሳሽ ጫላ አለሙና 19ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ አለሙ ዋስትና በሚያስከለክል አንቀጽ መከሰሳቸውን በመጠቆም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ጠይቋል።
በመሆኑም ሶስቱም ተከሳሾችን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩና በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ እንዲያስገቡ ነው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው።
በቀጣይም ፖሊስ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ለመጋቢት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።