አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፖሊስን ዘመናዊ ሰራዊት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ብቃትና ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዲስ የተገነባውን የፌዴራል ፖሊስ የእዝ መቆጣጠሪያ ማዕከል ጎብኝተዋል።
በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍም ፖሊስ እንደ ህግ አስከባሪ ህግ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ እንደ ወንጀል መርማሪ የወንጀል ምርመራ ክህሎት ያለው፣ የስነ-ባህሪ ጥናት ያጠና፣ የስነ ባህሪ ሳይኮሎጂን ጠንቅቆ የሚያውቅ ለማድረግ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም እንደ ሰራዊት ወታደራዊ ብቃት ያለው፣ እንደ አድማ በታኝ የተሟላ ተክለሰውነት ያለው፣ እንደ ደህንነት ተቋም መረጃ መሰብሰብና መተንተን የሚችል፣ ዘመኑን ለመዋጀት ቴክኖሎጂ ብቃትና ግንዛቤ ያለው፣ ዐሻራ፣ ዲ.ኤን.ኤ. እና ዲጂታል ፊርማ እንዲሁም ዲጂታል ፎረንሲክ መተንተን የሚችል ዘመናዊ ሰራዊት እንዲሆን የተጀመረው ሪፎርም እንደሚቀጥልና መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንሚያደርግም አስታውቀዋል።
ማዕከሉ የወንጀል መከላከል ስራዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚሰራበት እና ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ማስረጃ የሚሆኑ መረጃዎች የሚሰበሰብበት ነው።
በማዕከሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች በተከላቸው ቋሚ ካሜራዎች፣ በመኪና እንዲሁም በሰው እና በየትኛውም አስፈላጊ ቦታ በሚቀመጥ ካሜራ አማካይነት በከተማዋ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ 24 ሰዓት እየሰራ ይገኛል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሲ ሲ ቲቪ ካሜራ መጠቀም የጀመረው ከ15 ዓመት በፊት ነበር።
በወቅቱ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ መስቀል አደባባይ ነበር ካሜራ የተገጠመው።
አሁን አሮጌው ካሜራ እንዲቀየር ያደረገው ካሜራው አናሎግ በመሆኑ እና ምሽት ላይ ምስል በጥራት ስለማይቀርጽ መሆኑ ተገልጿል።
አዳዲሶቹ ካሜራዎች በቀንም ሆነ በማታ ምስልን በጥራት ያስቀራሉ ነው የተባለው።
በዓላዛር ታደለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!