የሀገር ውስጥ ዜና

በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ልዑካን ቡድን በዶሃ ፎረም በመካፈል ላይ ይገኛል

By Mekoya Hailemariam

March 27, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ልዑካን ቡድን በኳታር “ዶሃ ፎረም” በመካፈል ላይ ይገኛል።

የዶሃ ፎረም ዓለም አቀፋዊ የውይይት መድረክ ሲሆን ዘንድሮ “ወደ አዲሱ ዘመን ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ ለ20ኛ ጊዜ በኳታር ዶሃ እየተካሄደ ነው።

በአሁን ጊዜ የዶሃ ፎረም በዓለማችን እያጋጠሙ ባሉ ዓለም አቀፍ ይዘት ባላቸው ቁልፍ ፈተናዎች እና ወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ግልፅ አቅጣጫ እና ተግባር ተኮር ምክረ ሃሳቦችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ የሚመራው ልዑካን ቡድን ሃገራችንን በመወከል በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ ሲሆን፥ በተመሳሳይ በመድረኩ የበርካታ ሃገራት መሪዎች እየተካፈሉ መሆኑን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።