የሀገር ውስጥ ዜና

ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑ ተገለጸ

By Meseret Awoke

March 29, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2014/15 የሰብል ዘመን የሚውል ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ከውጭ ሀገር የተገዛ የአፈር ማዳበሪያ ከጥር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

ለዘንድሮው የምርት ዘመን የሚውል 12 ሚሊየን 876 ሺህ 623.5 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ እንደሆነ ነው ኮርፖሬሽኑ የገለጸው።

በየዓመቱ በግብርና ሚኒስቴር ተጠንቶ በሚቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት ኮርፖሬሽኑ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ እያስመጣ እንደሚገኝ ጠቁሟል። ለምርት ዘመኑ ከተያዘው የማዳበሪያ መጠን ውስጥ እስከ ዛሬ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም. ድረስ 3 ሚሊየን 724 ሺህ 30 ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ የደረሰ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ 2 ሚሊየን 863 ሺህ 890 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ማዳበሪያውን በመርከብ አጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ ካራገፈ በኋላ፣ በከባድ ተሽከርካሪዎችና በባቡር ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው ድልድል መሰረት በክልሎች ለሚገኙ ማህበራት እንደሚያሰራጭም ነው የተጠቆመው።

በማህበራቱ አማካይነት ማዳበሪያው አርሶ አደሮች ጋር እየደረሰ እንደሆነም ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት በአማካይ ከጅቡቲ ወደብ በየቀኑ ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እየተጓጓዘ እንደሆነ ኮሚሽኑ ገልጾ፥ እስከ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም ድረስ ጅቡቲ ወደብ 860 ሺህ 140 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ያልተጫነ ይገኛል ብሏል።

በተጨማሪም መጋቢት 29/2014 ዓ.ም 580 ሺህ 120 ኩንታል እንዲሁም ሚያዝያ 1/2014 ዓ.ም. 600 ሺህ ኩንታል በአጠቃላይ 1 ሚሊየን 180 ሺህ 120 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች ጅቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ ይጠበቃል ሲል ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!