የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በ60ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓሲፊክ ሃገራት የፓርላማ ምክር ቤት እየተሳተፈች ነው

By Meseret Awoke

April 01, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው 60ኛው የአፍሪካ፣ የካሪቢያን እና የፓሲፊክ ሃገራት የፓርላማ ምክር ቤት እየተሳተፈች ነው፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ትናንት በይፋ በተከፈተው 60ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና የፓሲፊክ ሃገራት የፓርላማ ጉባኤ ተሳትፏል።

ድርጅቱ ጉባኤውን እያካሄደ ያለው በተለያዩ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በተካሄዱ የተለያዩ የኮሚቴዎች ስብሰባ ውጤቶች ሲሆን ፥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅዕኖዎችን መቆጣጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ በመመካከር እና ድርጅቱ ከዓለም እውነታ ጋር የተስማማ እንዲሆን ማድረግን በመሰሉ ጉዳዮች ዙሪያም እየመከረ ነው።

የድርጅቱን ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት ረገድ ብቁ፣ ቀልጣፋ፣ እና ገለልተኛ ለማድረግ ኢትዮጵያ የበኩሏን ሚና ለመጫወት ያላትን የማይናወጥ አቋም አቶ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል።

በክለሳ ላይ ያለውን የጋራ የፓርላማ ምክር ቤት የአሰራር ደንቦችን የሚያሻሽሉ ጠቃሚ ጉዳዮችንም ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ኮሚቴው ከጉባዔው ቀደም ብሎ ባደረገው የዝግጅት ስብሰባ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ፥ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለጉባዔው አባላት አብራርተዋል።

በፈረንጆቹ 2020 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ይህ የመጀመሪያው በአካል የተደረገ ጉባኤ ነው ተብሏል።

ድርጅቱ አፍሪካን፣ ፓሲፊክን እና ካሪቢያንን የሚሸፍኑ 79 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን ፥ ዋና መቀመጫውን ብራሰልስ አድርጓል።

ኢትዮጵያም የድርጅቱ መስራች አባል ሃገር መሆኗ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!