የሀገር ውስጥ ዜና

በህገወጥ ገንዘብ መያዝ እና የአደንዛዥ እፅ ማዘዋወር ወንጀል የተጠረጠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው

By Alemayehu Geremew

April 01, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገወጥ ገንዘብ መያዝ እና የአደንዛዥ እፅ ማዘዋወር ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ፅኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተወሰነባቸው

በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ በመግባት መኖር የውጭ ሀገር ገንዘብ መያዝና የአደንዛዥ እፅ ማዘዋወር ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው በፅኑ እስራትና በገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ተወሰኖባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር የሚያስችል የፀና የመግቢያ ቪዛም ሆነ የመኖርያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሚኖሩ ህገ-ወጥ ገንዘብ እና እጽ አዘዋዋሪዎች እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው በፅኑ እስራትና በገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል ።

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የኢኮኖሚ ወንጀል ችሎት ነው ።

ቅጣት የተጣለባቸውም ÷ 1ኛ ኖንስ ሳሙኤል፣ 2ኛ ማይክል ኤዜካፎር እና 3ኛ ቪንሲንት ዲኬ የተባሉ ናይጀሪያዊ ተከሳሾች ሲሆኑ የወንጀል ህግ አንቀፅ 525 (1)(ለ)߹የብሔራዊ ባንክን ለማቋቋም የወጣውን 591/2000 አንቀፅ 202 እና አንቀፅ 4.3.1 አንዲሁም በ1995 የወጣውን የኢምግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354 አንቀፅ 3(1) ߹ 20(1)(ሀ) በመተላለፋቸው ነው በዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው ።

ሶስቱም ተከሳሾች መጋቢት 21/2013 ዓ.ም ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሰሚት “30 ሜትር” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በተደረገባቸው ድንገተኛ ፍተሻ እና በተደረገባቸው ብርበራ በአጠቃላይ 179 ጥቅል የኮኬይን እፅ እና 11 ሺህ 615 የአሜሪካን ዶላር ይዘው እንደተገኙ ተገልጿል፡፡

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር የሚያስችል የፀና የመግቢያ ቪዛም ሆነ የመኖርያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው የመኖርያ ቤት ተከራይተው የተገኙ በመሆኑ ፤ተከሳሾች በፈፀሙት የፀና የሞኖርያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባትና መኖር ߹ ህገ ወጥ ገንዘብ በመያዝና አደንዛዥ እፅ ማዘዋወር ወንጀል በመፈፀማቸው ነው በዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው።

ፍርድ ቤቱ ም እንደ ተከሳሾች የወንጀል ተሳትፎና የተለያዩ የቅጣት ማቅለያዎችን ከግምት ውስጥ አስገብቶ የሚከተለውን የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል።

1ኛ ተከሳሽ በ5 ዓመት ፅኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር፣ 2ኛ ተከሳሽ በ8 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራትና እና በ30 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ በ7 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እስራትና በ30 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ መወሰኑን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡