አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በፋይናንስ አቅርቦት ግንባታቸው ለጊዜው ቆመው የነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች እና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት ያስሚን ወሀብረቢ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት÷ 80 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ 5 ነጠብ 4 ቢሊየን ብር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦንድ ብድር የቀረበ ሲሆን ከ80 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች 70 በመቶውን አጠናቆ ለማስረከብ የሚያስችል 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት ተፈቅዷል።
የአስተዳደሩ ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በበኩላቸው ከ87 እስከ 97 በመቶ የግንባታ ሂደታቸው ለጊዜው የቆመ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገኘውን ብድር በመጠቀም ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ሰዎች ሊኖሩባቸው የሚችሉ መሰረታዊ ነገሮችን በማሟላት ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ርብርብ እንደሚደረግም ዋናዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በበላይ ተስፋዬ