አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
በክልሉ በተደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ወቅት ከህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች እና ሊወሰዱ በሚገቡ የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ከክልሉ የመንግስት ቢሮ ማኔጅመንት ኮሚቴና አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በጅግጅጋ ከተማ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት÷ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድን ጨምሮ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሒም ኡስማን እና የሶማሌ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሐላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ ተገኝተዋል።
ህብረተሰቡ በዋናነት የኑሮ ውድነትን፣ ህገወጥ የነዳጅ ዝውውር፣ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረትና፣ የከተማ ቤት ኪራይ ዋጋ ኢ -ፍትሐዊነት እና የግብርና ምርት ውጤቶች ማነስን በሚመለከት በተደረጉ ውይይቶች ጥያቄ ማንሳቱ ተገልጿል፡፡
የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም የህግ የበላይነት አለመስፈን ተደጋግመው የተነሱ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
በክልሉ ብልፅግና ፓርቲ የማስተካከያ አቅጣጫዎች እንደተቀመጡ የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስዳድር አቶ ኢብራሒም ዑስማን÷ ከክልል እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅር ማጠናከር፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን አሰራር ቀልጣፋና የተሟላ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
የምርት እጥረትና የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ወንዞችንና የዝናብ ወቅትን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ ግብርናው ላይ ትኩረት ማድረግ እና የከተማ ግብርናን ማስፋፋት፣ የስራ ዕድል ፈጠራን በስፋት ማጠናከር እና የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው÷ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሁሉም የመንግስት አመራር ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው÷ በተለይም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከቀድሞው በተለየ አገልሎት አሰጣጣቸውን ማስተካከል እና ግልፀኝነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ከመንግስት ጋር እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ ክልሉ በቀጣይ የህዝቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ፣ በውሀና በአነስተኛ መስኖዎች ላይ እንደሚያተኩር ማስረዳታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡