የሀገር ውስጥ ዜና

በድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ግብርና የህዝብ ንቅናቄ ማብሰሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ

By Alemayehu Geremew

April 07, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ግብርና የህዝብ ንቅናቄ ማብሰሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር እንደገለጹት÷ የከተማ ግብርና የአትክልትና ልማት ስራዎች የህዝብ ንቅናቄ ፕሮግራም ህብረተሰቡ ባለው አቅም በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ በሚውሉ ቁሳቁስ አማካኝነት ወደ ላይ የሚዘረጉ የአትክልት ቦታዎችን በማዘጋጀት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

ይህም በምግብ ራስን መቻልና በራስ አቅም የመልማት ቁርጠኝነትና ድህነትን በሥራ የማሸነፍ ተምሳሌት እውን ለማድረግ ይረዳል ነው ያሉት፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ባላቸው ጓሮ ወይም በአካባቢያቸው በሚገኝ ቁሳቁስ ተጠቅመው የጓሮ አትክልቶችን በመትከልና በመንከባከብ ምግባቸውን ከጓሮ መጠቀም መጀመር አለባቸው ብለዋል፡፡

ሰፋፊ የአትክልት ስፍራ ያላቸው የመንግስት እና የግል የትምህርት ተቋማት፣ ሴክተር ተቋማት የንቅናቄው ዋና ተዋናይ ሆነው ለህብረተሰቡ ግንዛቤን በመፍጠር የተጀመረውን የከተማ ግብርና ንቅናቄ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውን የድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡