የሀገር ውስጥ ዜና

የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

By Meseret Awoke

April 08, 2022

 

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአስተባባሪና የማኔጅመንት አባላት የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ፥ በሀገራችን የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት በእውቀት ላይ የተመሠረተ የግጭት መከላከል ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ የሚገኙ ግብዓቶችን በማካተት ስትራቴጂውን በቀጣይ የሥራ መመሪያ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል።

የስትራቴጂ ሰነዱን ለመድረኩ ያቀረቡት አቶ ብዙነህ አሰፋ ፥ የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ዋና ዓላማ ስትራቴጂውን በመጠቀም በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የተፈጸሙትንና ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ ግጭቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፍታት ነው ብለዋል።

አያይዘውም ፥ የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ በኢትዮጵያ ሰላምን በመገንባት፣ ግጭቶችን በመፍታትና የግጭት ምልክቶችን ቀድሞ በመከላከል ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴና የጽህፈት ቤቱ ማኔጅመንት አባላት በስትራቴጂ ሰነዱ ላይ መክሮ ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጥበታል ተብሎ እንደሚታሰብ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!