አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረቁ ስራ ፈላጊ ወጣቶች የመስሪያ ሼዶችን አስረክቧል፡፡
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በርክክቡ ወቅት ÷ በከተማዋ በ2014 በጀት አመት ከ25 ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት የስራ እድል ለማመቻቸት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለ410 ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረቁ ስራ ፈላጊ ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር የማምረቻ ሼድ ማስረከቡንም ነው ከንቲባው ያስረዱት።
በቀጣይም አስተዳደሩ በበጀት አመቱ የያዘውን እቅድ ለማሳካት አስፈላጊውን የፋይናንስና የመስራያ ቦታ የማመቻቸቱን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለፁት።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በበኩላቸው ÷አስተዳደሩ የፈጠረው የስራ እድል በተለይም በከተማ ግብርና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራ በተለያዩ አምራች ዘርፎች ላይ መሆኑ ውጤቱን ይበልጥ ተጨባጭ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዞች ልማት እና የስራ እድል ፈጠራ መምሪያ ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ዳሪሞ÷ አስተዳደሩ 30 ሚሊየን ብር በዕለቱ የማምረቻ ሼድ ለተረከቡ ወጣቶች ብድር እንዳመቻቸላቸው አስረድተዋል።
በዕለቱ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችም አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ያደረገውን ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡