የሀገር ውስጥ ዜና

ሠላም የማይነጥፍ የሰው ልጆች ኃብት መሆኑን የኮንሶ እና ኧሌ አባቶች ተናገሩ

By Amare Asrat

April 13, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮንሶ ዞን እና በኧሌ ልዩ ወረዳ መካከል የተፈጠረውን ግጭት በማብረድ ሠላም ለማምጣት በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

አምስተኛው ዙር የሁለትዮሽ ለሠላም የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅትም በሁለቱም ወገን ግጭት ቆሞ እና እርቅ ተፈጽሞ አርሶ አደሩ ወደ ቀድሞው እርሻና ልማት ሥራው እንዲመለስ አባቶች ጠይቀዋል።

በመጨካከን የተፈጠረው ግጭት እንደጎዳቸው የተናገሩት የሃገር ሽማግሌዎቹ፥ ሠላምና የትናንት አብሮነት ናፍቆናል፣ ቤተሰባዊነትን የሚያደፈርሱ ኃይሎች ለህግ ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

የኮንሶ ዞን እና የኧሌ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው የሁለትዮሽ ሠላምን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከክልሉ ፀጥታ ቢሮ የተገኙት ሻለቃ አያና እንደተናገሩት የጋራ ሀብት የሆነውን ሠላም በማስፈን እንደቀድሞው በሠላም መኖር እንደሚገባ አስረድተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የደረሰው የንብረት ውድመት እንደጎዳቸው በመጥቀስ ለሠላም በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስትም ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የችግሩ መንስኤ የሆነውን የእርሻ መሬትና የወሰን ጉዳይን እንዲፈታ ጠይቀዋል።

በውይይቱ ወቅት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራ በመስራት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስና ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ሥራ መስራት እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በውይይቱ የአካባቢ ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የቀበሌ፣ የዞንና ልዩ ወረዳ አመራር እና የክልል ፀጥታ ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።