የሀገር ውስጥ ዜና

የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

April 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማን ሰላም እና ፀጥታ ለማስጠበቅ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተመላከተ፡፡

በአዲስ አበባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አዘጋጅነት በከተማዋ ሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና እና ኤምባሲዎች መገኛ መሆኗን የጠቀሱት የከተማ አስተዳደሩ ሰላም እና ፀጥታቢሮ ሀላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ፥ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማዕከል መሆኗን ታሳቢ ያደረገ የሰላም እና ፀጥታ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በከተማ አስተዳድሩ የፀጥታ ተቋማትን የማጠናከር፣ ህዝቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን የማድረግ፣ ወንጀልን የመከላከል፣ ፈጣን ምላሽ የመስጠት፣ ከተቋማት እና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት የመስራት እና የአገልግሎት አሰጣጥን የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አራጋው እንደገለጹት፥ ባለፉት ጊዜያት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በተሰራ ስራ በርካታ ህገወጥ ስራዎችን ለማስቆም ተችሏል።

የጦር መሳሪያ እና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች የወንጀል ድርጊቶችን ለመቆጣጠር ተችሏልም ብለዋል።

በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ወንጀል የመከላከል ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር፥ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ጠንካራ የፖሊስ፣ የደህንነት እና የፀጥታ ተቋም መገንባት እንደሚገባ ገልጸው፥ ለተቋማቱ ውጤታማነትም የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለህዝቡ ተሳትፎ ውጤታማነት በቅርቡ በከተማዋ የታየው እና በህግ ማስከበር ዘመቻው ህብረተሰቡ የተሳተፈበት የሰላም እና ደህንነት ጥበቃ ስራ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከተማዋ የሰላም ተምሳሌት እንድትሆን ከተፈለገ የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በምንይችል አዘዘው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!