አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በእርዳታ ለገቡ ቁሳቁሶች ለመጋዘን ኪራይና ለአገልገሎት ክፍያ ይውል የነበረ 25 ሚሊየን ብር ወጪ መሰረዙን ገለጸ።
አየር መንገዱ በካርጎ መጋዘን የተከማቹ የድጋፍ ቁሳቁሶችንም በዛሬው ዕለት ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክቧል።
በርክክብ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው÷አየር መንገዱ ከሥራው ጎን ለጎን በማኅበራዊ ሃላፊነትም የላቀ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ÷በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድርቅና ጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የሚደርስ 114 ሺህ 400 ኪሎ ግራም የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን መላኩን ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱም የድጋፍ ቁሳቁሶቹን በመረከብ በጭነት ማከማቻ መጋዘኖች ሳይበላሹ ጥራታቸውን እንደተጠበቁ እንዲቆዩ ማድረጉን ገልጸዋል።
የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሐሰን ÷ የእርዳታ ቁሳቁሶቹን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለማጠናከር በማሰብ ”ኢቲ ፋውንዴሽን” ማቋቋሙ ታውቋል።