የሀገር ውስጥ ዜና

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በአንድ ቢሊየን ብር በጀት የካንሰርና ኩላሊት ህክምና ማዕከል እንደሚገነባ አስታወቀ

By Meseret Awoke

April 16, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በአንድ ቢሊየን ብር በጀት የካንሰርና የኩላሊት ህክምና ማዕከል ለማስገንባት ዝግጅት መጀመሩን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በ2022 የግብርና እና ጤና-መር የልህቀት ማዕከል ለመሆን በያዘው እቅድ መሰረት በጤና ስራ ላይ አትኩሮ ለመስራት የያዘው ፕሮጀክት ወሳኝ እንደሆነ ተመላክቷል።

ከሦስት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በላይ ከሚጠይቀው ከዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ የልህቀት ማዕከልነት እቅድ ውስጥ ለካንሰርና ኩላሊት ህክምና ማእከሉ ወደ አንድ ቢሊየን ብር በጀት ይጠይቃል ተብሏል።

የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ልዩ ሆስፒታል እየሰራ የሚገኘውን ሁለ ገብ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በሚመለከት ዛሬ ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ ይፋ የተደረገው የማዕከሉ ፕሮጀክት የበለጠ ስራዎችን ለመስራት ያስችለዋል ተብሏል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በሰጡት ማብራሪያ፥ የሚገነባው የካንሰርና ኩላሊት ህክምና ማዕከል ደረጃውን የጠበቀና የኩላሊት ንቅለ ተከላን ለመጀመር የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቀጣይ ዓመት ግንባታው ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት፥ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ልዩ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አወቀ ወዳጆ እንዳሉት፥ በጤናው ዘርፍ ላይ ሰፋፊ አሰራሮችም የተዘረጉ ሲሆን በወሊድ ምክንያት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለማስቀረ ከቤት እስከ ሀኪም ቤት ክትትል ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችም ተጀምረዋል።

የመድሃኒት አቅርቦትን ለማስፋትም በዞኑ ባሉ ከተሞች መድሃኒት ቤቶችን ለመክፈት ዝግጅት ተደርጓል ነው የተባለው።

በሃይለየሱስ ስዩም

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!