አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን በተመለከተ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልእክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዶክተር ዐቢይ በመልእክታቸው፥ ዐድዋ በየትውልዱ እየተመነዘረ ለብልፅግና ጉዟችን ልንጠቀምበት የምንችለው ትልቅ ሃብታቸን ነው ብለዋል።
አድዋ ኢትዮጵያዊያን አንድም ብዙም መሆናችንን ያሳየንበት ታሪክ ነው፤ በባህል፣ በቋንቋ፣ በብሄር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በእምነት የየራሳችን ማንነት አለን። ይህ ማንነታችን በሀገራችን ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ታግለናል፣ እንታገላለን። ከዚህ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊ ያሰኘን አንድነትም አለን ሲሉም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን በተመለከተ ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
እንኳን ለ124ኛው የዐድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ።
ዐድዋ በየትውልዱ እየተመነዘረ ለብልፅግና ጉዟችን ልንጠቀምበት የምንችለው ትልቅ ሃብታቸን ነው።አድዋ ኢትዮጵያዊያን አንድም ብዙም መሆናችንን ያሳየንበት ታሪክ ነው። በባህል፣ በቋንቋ፣ በብሄር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በእምነት የየራሳችን ማንነት አለን። ይህ ማንነታችን በሀገራችን ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ታግለናል፣ እንታገላለን። ከዚህ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊ ያሰኘን አንድነትም አለን።
ጣሊያኖች ወደ አድዋ ሲመጡ የታያቸው ልዩነታችን ነው። በልዩነታችን ላይ ሰርተው ኢትዮጵያውያንን በማዳከም ቅኝ ግዛትን ሊጭኑብን አስበው ነበር። የኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ጸጋዎች መከፋፈያ የሚሆኑ መስሏቸው በተለያየ መንገድ ሞክረው ነበር። ወደ አድዋ ሲመጡ ግን ያሰቡትን አላገኙም። ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ በሉዓላዊነታቸው ጉዳይ በነጻነታቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሆኑን አሳዩ። ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ጸጋ እንጂ መለያየት እንደሌላቸው አድዋ አሳያቸው። ኢትዮጵያውያን ኅብራዊ አንድነት እንዳላቸው አድዋ መሰከረ።
ልዩ ልዩ ጸጋዎቻችንን የመለያያ ምክንያት የማድረግ ዘመቻ ፈጽሞ እንደማይሳካ አድዋ ህያው ምስክር ነው። ኢትዮጵያውያን በአድዋ ዘመቻ ዋዜማ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ነበሯቸው። ከወቅቱ መሪዎች ጋር በሁሉም ነገር የሚስማሙ አልነበሩም። የዘመኑ አስተዳደር ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ አልነበረም። እነዚህን ሀገራዊ ችግሮች አቀጣጥለው ሀገር የማዳከሚያ መሳሪያ ለማድረግ ጣሊያኖች ሞክረዋል። ቁስሉን ለማዳን ሳይሆን በቁስሉ ለማስለቀስ ጥረዋል። ኢትዮጵያውያን ግን ችግራችንን እንፈታለን፤ ሀገራችንን እንጠብቃለን ብለው አልተቀበሉትም።
ጥያቄዎች ሁሉ የሚመለሱት ሀገር ስትኖር መሆኑን ኢትዮጵያውያን ያውቁ ነበር። ኢትዮጵያዊን ለቁንጫ ብለው ቤት የሚያቃጥሉ፣ ለአረም ሲሉ ማሳውን የሚያጠፉ አልነበሩም።
ኢትዮጵያዊን ሀገራቸውን በተመለከተ ዘላቂ መርህ አላቸው። ዋልታና ማገሩን እጠብቃለሁ፤ ውስጡንም አጸዳለሁ የሚል፣ ቤቱ ቤት ሆኖ እንዲኖር ዋልታና ማገሩን ማጥበቅ ያስፈልጋል። ቤቱን ለማጽዳት መጀመሪያ ቤቱ ቤት መሆን አለበት። ቤቱ በሌለበት የቤት ጽዳት አይኖርም። ቤቱ ግን ሊቆሽሽ ወይም ተባይ ሊያፈራ ይችላል። ቤቱን እያጠበቅን እያጸናን ውስጡን ደግሞ እናጸዳለን።
ዓድዋ ሌላም ትምህርት ሰጥቶናል። ችግሮቻችንን እንዴት ማየት እንዳለብን። አጼ ምኒልክ ለአድዋ ዘማቾች ለዘመኑ ችግር በቂ ዝግጀት አድርገው ነበር። ያዘጋጇቸው መድፎች ከጣሊያን መድፎች የተሻሉ ነበሩ።
ጣልያን ወታደሮቹን ካንቀሳቀሰበት ዓቅም በላይ ህዝቡን ለማንቀሳቀስ ችለዋል። የት ቦታ፣ እንዴት ጠላቶቻቸውን ገጥመው ሊያሸንፉት እንደሚችሉ ዓቅደዋል። የዓድዋ ድል የዚህ የላቀ ዝግጅት ውጤት ነው።
ከአርባ አመታት በኋላ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ልንቋቋመው ያልቻልነው በአድዋ ዘመቻ ያደረግነውን ነገ ተኮር ዝግጅት ስላላደረግን ነው።
ጣሊያን በአየር ሲመጣ በመሬት ገጠምነው። ጣሊያን የምድር ላይ ዘመቻዎቹን አዘምኖ ሲመጣ እኛ ያለንን ይዘን ጠበቅነው ከዘመኑ ቀድመን አልተገኘንም።
ዛሬ ከትላንት የተለየን መሆናችን ብቻ በቂ አይደለም፤ ስልጣኔ ማለት ከነገ መቅደም ነው። ነገ ከሚመጣ ችግር በልጦ መገኘት ነው። ከአድዋ የምንማረው አንዱ ትልቁ ትምህርት ይህ ነው። ትላንት ለገጠመን ችግር መፍትሄ መስጠት ችሎታ ነው። ዛሬ ለሚገጥመን ችግር መፍትሄ ማስቀመጥ ብልሃት ነው። ወደ ፊት ከሚመጣ ችግር በልጦ መገኘት ግን ጥበብ ነው።
የአድዋ ዘመቻ የጦርነት ዘመቻ ብቻ አልነበረም የቴክልኖሎጂ ዘመቻ ፤ የዲፕሎማሲ ዘመቻ፣ የትዕግስት ዘመቻ፣ የፖለቲካ ዘመቻ፣ የሎጂስቲክ ዘመቻ፣ የፍቅርና የይቅርታ ዘመቻም ጭምር ነበር። በዘመኑ የተሻሉ መሳሪያዎችን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ለዝግጅት ጊዜ ለማግኘት እንዲቻል የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቷል። ችግርን በትክክለኛው ጊዜና ሁኔታ ለመግጠም ሲባል በፈታኝ ትዕግስት ውስጥ ታልፏል። ለዚያ ሁሉ ሰራዊት የሚሆን ስንቅና ትጥቅ ለማዘጋጀት ህዝቡን አንቀሳቅሰዋል። ውስጣዊ ቅራኔዎች አገራዊ አደጋ እንዳያስከትሉ የዕርቅና የመቻቻል ስራዎች ተሰርተዋል።
ዛሬም እንደ አገር የገጠመንን ችግር ለመፍታት የአድዋ ዘማቾች የተጠቀሙበትን ዘርፈ ብዙ መፍትሄዎች መጠቀም አለብን። ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ ዲፕሎማሲ ትግል ማድርግ፣ በትግዕስት ጊዜ መስጠት፣ የፖለቲካ መፍትሄዎችን መስጠት፣ አቅም ማጠራቀም፣ በፍቅርና በይቅርታ መንገድ መጓዝ፣ ሌሎችም ያስፈልጉናል።
የዓድዋ ዘመቻ ድል እንዴት ማጠናቀቅ እንደሚቻል ያስተማረ ትልቅ ታሪካችን ነው። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው የመጣባቸውን ወራሪ መክተዋል። መክተዋል ብቻ ሳይሆን አሳፍረው መልሰዋል።
ነገር ግን የውጭ ጠላታቸውን ድል ያደረጉበትን አቅም የራሳቸውን ጉዳይ ለመፍታት አላዋሉትም። አንድ ታላቅ አገራዊ ድል ካገኘን በኋላ ውሰጣዊ ጥንካሬያችንን በድላችን ልክ ለማድርግ ካልሰራን ድላችንን የሚያሳጣን እድል ሊገጥመን ይችል ይሆናል። ለምን አሸነፍን? ያሸነፍንበት ሚስጥር ለውስጣዊ የአገር ግንባታ እንዴት እንጠቀምበት? የዛሬውን ጠላት አሸንፈን ነገር ግን ኢትዮጵያን ነገ ከሚመጣው ጠላት የተሻለች አድርገን እንዴት እናቆያት?
እነዚህን ጉዳዮች አለማየት ከአድዋ ድል ዐርባ ዓመት በኋላ በማይጨው ዘመቻ የገጠመንን እንዲገጥመን መፍረድ ነው። ያ እንዲሆን ዛሬ ፈጽሞ አንፈቅድም። በዐድዋ ድል የተነሳ ብዙ ህዝቦች ሮጠው ቀድመውናል። የተሻለ ሀገረ መንግስት ገንብተዋል፡ የተሻለ ብሄረ መንግስት አዳብረዋል። ዴሞክራሲያቸውን፣ የፍትህ ስርዓታቸውንና ኢኮኖሚያቸውን አዘምነዋል። ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ሲቆረጥ ለምን ዝም እንላለን?
የመደመር ጎዳና ኢትዮጵያ የዐድዋ ድሏን በሚመጥን ደረጃ እንድትጓዝ የተገነባ መንገድ ነው። ለዐድዋ ድላችን የሚመጥነው የኢትዮጵያ ከፍታ ብልጽግና ነው። እኛ ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች የመጣን የአድዋ ዘማቾች ነን። አንድ ሆነን ጠላታችንን ተዋግተን ድል እንዳደረግነው ሁሉ አንድ ሆነን ሀገር እንገነባለን። አንድ ሆነን ሀገራችንን ወደ ብልጽግና እናደርሳለን።
የትናንት እናቶቻችንንና አባቶቻችንን ድል ዛሬ እንዳከበርነው ሁሉ የእኛንም ድል ነገ ልጆቻችን ያከብሩታል። እነርሱ የቀኝ ግዛትን ቀንበር ሰብረው ነው። እኛ ደግሞ የድህነትን ቀንበር እንሰብራለን። እነርሱ ነጻ ሀገር ፈጥረዋል፤ እኛ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሀገር እንፈጥራለን። እነርሱ በመደመር ተጉዘው ድል አስገኝተዋል። እኛም በመደመር ተጉዘን የብልጽግናን ድል እናስገኛለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራ እና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!