አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወንጀልን በሌላ ወንጀል ለማረም መሞከር ሕገ ወጥነት ነው ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡
ጉባኤው በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ÷በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈፀመውን ሕገ ወጥና የወንጅል ተግባር አውግዛለሁ ብሏል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈፀመውን ሕገ ወጥና የወንጅል ተግባርን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በእጅጉ ያወግዛል፡፡
ተግባሩ በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነትየሌለው ከመሆኑም በላይ ደረቅ ወንጅልና በህግ ሊያስጠይቅ የሚገባው ተግባር መሆኑንምጉባኤያችን በጽኑ ያምናል::
ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የተፈፀመወን አስነዋሪ ተግባርን አስመልክቶ ጉባኤያችን በትናንትናው ዕለት ዕለት ባወጣው መግለጫ ተግባሩን አምርሮ በማውገዝ ጥፋትን በጥፋት፣ ወንጀልን በወንጀል ለማረም የሚደረግ ሙከራ እንዳይኖር ማስገንዘባችን ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ ትናንት በሆነው ሁሉ አዝነንሳንጨርስ ይህ መከሠቱ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡
ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምን የሚሰብኩ፣ ትህትናን የሚስተምሩና ለሌሎች ስለመኖርና መስዋዕት ስለመክፈል የሚገዳቸው እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በሃይማኖት ስምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈፀመው ሁሉ ሕገ ወጥና ደረቅ ወንጀል እንደሆነ ታውቆ መንግስት ሕግና ስርኣትን እንዲያስጠበቅ ጉባኤያችን አበክሮ ይጠይቃል፡፡ መንግስት ሕግና ስርኣትን ለማስፈፀም እንዲችል ቀደም ብሎ ያወጣቸውን ህጎችን ሁሉ ተፈፃሚ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙም ይሁን ሕዝበ ክርስቲያኑ በየትኛውም አካባቢ የተከሠተው ችግርና የደረሰው ውድመት ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለው መሆኑ በመገንዘብ አካባቢያቸውን በጋራ በመጠበቅ፣ ችግሮች እንዳይባባሱም አንዱ ሌላውን በመጠበቅ የበኩላችሁን እንዲወጡ እየጠየቅን ችግር ፈጣሪዎችንም በማጋለጥና አሳልፎ ለሕግ አካላት መስጠት እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ሀገራችሁንና ወገናችሁን ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጥ ሁሉንምተግባር በማስተዋል እንድትከውኑ እየጠየቅን በሃይማኖት ስም የሚደረግ የጥላቻ ቅስቃሳን ባለማጋራት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!