የሀገር ውስጥ ዜና

ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

By Meseret Awoke

May 19, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የስምምነት ፊርማውን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ስመኝ ውቤ እና የኢትዮጵያ ጥራት፣ ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራቱ ተፈራርመውታል።

የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት በገለልተኛ አካል ሊመዘን እንደሚገባ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ስመኝ ውቤ ገልጸዋል።

የሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶችም ግዴታቸውን መወጣታቸው የሚረጋገጠው የአገልግሎት አሰጣጣቸው ጥራት በገለልተኛ አካል ተመዝኖ ሲረጋገጥ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሙት ምክትል ኮሚሽነሯ፥ ጥራት ያለው፣ ተደራሽና ፈጣን መንግስታዊ አገልግሎት ለዜጎች መስጠት የሲቪል ሰርቪሱ ግዴታ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ በበኩላቸው፥ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተቋማት ዓለም አቀፍ መስፈርትን በጠበቀ መልኩ ገለልተኛ በሆነ ተቋም መመዘን ይገባቸዋል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ደረጃ እንዲወጣላቸው ማድረጉ አገራዊ ኃላፊነት ካለበት ከአንድ ተቋም የሚጠበቅ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡