አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አየር ኃይል “ሰራዊት ሀገር እንጂ ብሄር የለውም ” ከሚለው የአስተሳሰብ ለውጥ ጀምሮ በአደረጃጀት በትጥቅና ስልጠና እንዲሁም በሰው ኃይል ግንባታ እራሱን እያደራጀና እያዘመነ እንደሚገኝ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ አየር ኃይል የማዕከላዊ አየር ምድብ በግዳጅ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የሰራዊቱ አመራርና አባላት የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ፕሮግራም አካሂዷል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የአድዋ ድል ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው እውቅናና ሽልማት እና የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ አየር ኃይሉ “ሰራዊት ሃገር እንጂ ብሄር የለውም “ከሚለው የአስተሳሰብ ለውጥ ጀምሮ በአደረጃጀት በትጥቅና ስልጠና እንዲሁም በሰው ኃይል ግንባታ እራሱን እያደራጀና እያዘመነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝና ሰሜን አየር ምድብ ላይ የፈፀመውን አረመኔያዊ ጥቃት ተከትሎ በተወሰዱት ተከታታይ ዘመቻዎች የአየር ምድቡ ጀግኖች መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል አኩሪ ታሪክ ሰርተዋል ብለዋል ዋና አዛዡ።
‘’በቀጣይም ለሚጠብቀን ማንኛውም ግዳጅ እራሳችንን ይበልጥ በማዘጋጀት ለኢትዮጵያ የሚመጥን ታላቅ አየር ኃይል የመገንባት ጉዟችንን አጠናክረን እንቀጥላለን’’ ሲሉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።
የማዕከላዊ አየር ምድብ አዛዥ ኮ/ል ወንዱ ኬዳ በበኩላቸው ፥ አየር ምድቡ ከተቋማዊ ሪፎርሙ ወዲህ በስልጠናና በጥገናው ዘርፍ ብሎም ዝግጁነትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ፥ በአየር ምድቡ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችና ምቹ የስራ ቦታን የመፍጠር ጅምሮችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ከተሰጣቸው የሰራዊት አባላት በሰጡት አስተያየት ፥ ዕውቅናና ሽልማቱ የበለጠ የስራ ሞራልና ተነሳሽነትን የሚፈጥርላቸው መሆኑን ገልፀው ፥ ወደ ፊትም የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።