አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጋር በጋራ የሚሰራቸው የሎጂስቲክስና አቪየሽን አገልግሎቶች ለሀገር ግንባታ ቁልፍ ናቸው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ተናገሩ፡፡
በአቪየሽንና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄና ከአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ወቅት ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር÷ የካርጎ አገልግሎት ቀልጣፋ መሆን ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ ጠቁመው ፥ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ስርዓት መኖር ደግሞ ሀገራችን ለተያያዘችው ፈጣን የዕድገት ጉዞ ቁልፍ መሆኑን አንስተዋል፡
አየር መንገዱ ካለው ሰፊ የካርጎ አገልግሎት አንፃር ተጨማሪ የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልገው ገልፀው፥ ይህን እውን ለማድረግ ከአየር መንገዱ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ በበኩላቸው÷ የዘመነ የሎጂስቲክስ ስርዓት ያላቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ቅልጥፍናን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር አጣምረው በመስራታቸው የተረጋጋ ኢኮኖሚ መገንባት መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላው ዓለም በሚያደርገው በረራ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን በማዘመንና ተጨማሪ የካርጎ ተርሚናሎችን በመጠቀም በአፍሪካ ምሳሌ ለመሆን እየሰራ መሆኑን አንስተው ፥ ይህን እውን ለማድረግም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ቁልፍ አጋር ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፥ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሚሰጣቸው ድጋፎች ለአየር መንገዱ አጠቃላይ አገልግሎት የማይተካ ሚና የሚጫወት በመሆናቸው ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት ያለንን ትስስር ማጠናከር ይገባል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡