አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካውያን ወጣቶች የሚፈጸሙ ጅምላ ግድያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀቡ መሆኑን ጥናት አመለከተ፡፡
የ”ማዘር ጆንስ የጅምላ ግድያ የመረጃ ቋት” የግድያ ወንጀሎችን በቁጥር አስደግፎ እንዳመላከተው ÷ በአሜሪካ ዕድሜያቸው 18 በሆናቸው ወጣቶች ዘንድ፥ ወታደሮች የሚታጠቋቸውን መሣሪያዎች የመታጠቅ እንዲሁም ሌሎች ዓይነት መሣሪያዎችን ገዝቶ የመያዝ ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡
በሳንዲ ሁክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተፈጸመው የጅምላ ግድያ 10ኛ ዓመት ከመታሰቡ ከወራት በፊት በሁለት ሣምንታት ልዩነት ሁለት የተለያዩ አሰቃቂ ጅምላግድያዎች ተፈጽመዋል ነው የተባለው፡፡
የአሜሪካ መንግስት በመሣሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መቆጣጠር እንዳልቻለና የሀገሪቷ የመሣሪያ ቁጥጥር ህግም የላላ እንደሆነ ዜጎች እየተናገሩ ነው፡፡
በፈረንጆቹ ግንቦት 14 አንድ የታጠቀ የ18 ዓመት ወጣት ኒውዮርክ ከተማ በሚገኝ ሱፐርማርኬት ውስጥ ገብቶ ሲገበያዩ የነበሩ 10 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡
ሕይወታቸውን ካጡ አሜሪካውያን ውስጥ አብዛኞቹ ሸማቾች የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው እንደነበሩም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በተመሳሳይ ከኒውዮርኩ የሱፐርማርኬት ጅምላ ግድያ 10 ቀናት በኋላ ሌላ ጠብመንጃ የታጠቀ የ18 ዓመት ወጣት በቴክሳስ ዩቫልዴ በሚገኘው ሮብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ የተኩስ እሩምታ ከፍቶ የ19 ተማሪዎችን እና የሁለት ሌሎች ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡
ዩቫልዴ በሚገኘው ሮብ ትምህርት ቤት የተፈጸመው ጅምላ ግድያ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከተፈጸሙት ግድያዎች በሟቾች ቁጥር ብዛት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
በአሰቃቂነቱ ቀዳሚ ነው የተባለለት በሳንዲ ሁክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተፈጸመው ጅምላ ግድያ ሲሆን በወቅቱ የ20 ተማሪዎች እና የስድሥት የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡
በዓመቱ በአሜሪካ ቴክሳስ ከተማ በወጣቶች ከተፈጸሙ የጦር መሣሪያ የጅምላ ግድያዎች ቀደም ብሎ ሌሎች 26 ግድያዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተፈጽመዋል ፤ ጉዳቶችና ሞቶችም መስተናገዳቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
የአዕምሮ ጤንነት ዕክል ያለባቸው ወጣቶች ደግሞ ለወንጀሉ መባባስ አስተዋፅኦዋቸው ቀላል አይደለም ነው የተባለው፡፡
በዩቫልድ ሮብ ትምህርት ቤት የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ በመቃወም በአሜሪካ የህዝብ ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ አለመረጋጋቶች እና ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተስተውለዋል፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞው ተስፋፍቶ ከካሊፎርኒያ እስከ ቬርሞንት ሰሜናዊ ተራሮች መድረሱ ነው የተሰማው፡፡
ለተጨማሪ መረጃ ቪዲዮውን ይመልከቱ፡-
በ35 የአሜሪካ ግዛቶች በሚገኙ ከ 200 በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል፡፡
ተማሪዎቹ በሮድ አይላንድ፣ ኒውዮርክ፣ ሚቺጋን፣ ሚዞሪ፣ እና ካሊፎርኒያ ጎዳናዎች ላይ በመገኘት በሮብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የደረሰውን ጅምላ ግድያ ተቃውመዋል፡፡
የፊታችን ዕሁድ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጅምላ ግድያ በተፈጸመበት ቴክሳስ ፣ ዩቫልድ ፣ ሮብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የሟቾችን ቤተሰቦች ያፅናናሉ ተብሏል፡፡