የሀገር ውስጥ ዜና

የሸገር አዲስ ገጽታ ፕሮጀክትን ለማበልፀግ በቀረቡት የዲዛይን ሀሳቦች ላይ አስተያየት ለመሰብሰብ ያለመ ኤግዚቢሽን ተከፈተ

By Meseret Awoke

May 28, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ያዘጋጀው ለሸገር አዲስ ገጽታ ፕሮጀክትን ለማበልፀግ ለውድድር የቀረቡት የዲዛይን ሀሳቦችን አስመልክቶ የህዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ ያለመ ኤግዚቢሽን ተከፈተ፡፡

ኤግዚቢሽኑ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን ፥ መስቀል አደባባይ በሚገኘው ዳያስፖራ ማዕከል ነው የተከፈተው።

የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሌንሳ መኮንን እንደተናገሩት ፥ የአዲስ አበባ መንገዶች ዳር የሚገኙ ይዞታዎች ማራኪ ገጽታ እንዲላበሱ ከማድረግ ባሻገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥቅማቸው እንዲያጎላ ሁሉን አቀፍ ዲዛይን ለማዘጋጀት ባለሙያዎች በስፋት ለማሳተፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

በአዲሱ ዲዛይን መሰረተ ልማቶች ተናበው ካለመስራት የሚከሰቱ ችግሮች እንደሚቀርፍም ዋና ዳይሬክተሯ ገልፀዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።

ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል ከቦሌ ሲቪል አቪዬሽን እስከ እንጦጦ እንዲሁም ከመስቀል አደባባይ እስከ አዲስ አበባ ከተማ መስተደድር ባሉ መንገዶች ላይ የሚገኙ የፌዴራል ይዞታዎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅማቸውን ለማሳደግ አጋዥ የሆኑ የልማት ሀሳቦችን ለማበልፀግ የመጀመሪያ ዙሪ የዲዛይን ጽንስ ሀሳብ ውድደሮችን አጠናቋል።

በመሆኑም በቴክኒካል ዳኞች ጥቅል ውጤት ከመሰጠቱ በፊት ለህዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ መክፈት ወስኗል።