አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የጓሮ ቡና ሽፋን የማሥፋት ስትራቴጂ ዳግም ንቅናቄ ” በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀምበር 10 ሚሊየን የቡና ችግኝ ለመትከል መታቀዱን የካፋ ዞን ቡና ፣ሻይ እና ቅመማ ቅመም ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ በዘንድሮዉ ዓመት 32 ነጥብ 9 ሚሊየን የቡና ችግኝ ለመትከል አቅዶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑንም አስታዉቋል።
በዞኑ ግብርና መምሪያ የቡና ፣ሻይ እና ቅመማ ቅመም ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ተክሌ ÷ በ2014 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት የተተከለዉን 15 ነጥብ 9 ሚሊየን የቡና ችግኝ መንከባከብ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ አጋማሸ የሚተከል 32 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኝ እንደተዘጋጀም ገልጸዋል።
ይህም በዞኑ 183 ሺህ ሄክታር የነበረዉን የጓሮ ቡና ሽፋን ወደ 190 ሺህ ሄክታር እንደሚያሳድገው ገልጸዉ እስካሁን ከ13 ሚሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአንድ ጀምበር ብቻ 10 ሚሊየን የቡና ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን የገለጹት አቶ ሞገስ ለዚህም 244 ሺህ የሚጠጋ ቋሚና ጊዜያዊ የጥላ ዛፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በአንድ ጀምበር 10 ሚሊየን የቡና ችግኞችን የመትከል መርሃግብሩም ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚከናወን ገልጸዉ በመርሃ ግብሩ ላይ ከ80 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
ተከላው የተለያዩ የመንግስትና የሃማኖት ተቋማት ባዘጋጁት ሥፍራ እንደሚከናወንም ነው የተገለጸው፡፡
ተከላው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አንዱ አካል መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አቶ ሞገስ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ደሬቴድ ዘግቧል።