የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራ ልዩ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በህልውና ዘመቻው ጉልህ አስተዋጽኦ ላደረጉ አባላቱ እውቅና ሰጠ

By ዮሐንስ ደርበው

May 31, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ልዩ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በህልውና ዘመቻው ጉልህ አስተዋጽኦ ላደረጉ አባላቱና የጦር መሪዎች እውቅና ሰጠ፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ልዩ ኃይል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል መሠለ በለጠ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።

የአማራ ልዩ ኃይል የህወሓት የሽብር ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ ክህደት ከፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በፈለገችው ግንባር ሁሉ እየገባ አያሌ ጀብዱዎችን መሥራቱ፣ የሽብር ቡድኑ ወደ አማራ ክልል ያደረገውን የወረራ ሙከራ በጀግንነት በመመከት ጠላትን ድባቅ መምታቱ በመርሐ ግብሩ ተገልጿል፡፡

የትህነግ የሽብር ቡድን በአማራ ክልል ላይ ዳግም ወረራ በፈፀመበት ወቅትም በጀግንነት በመነሳት ጠላቱን መደምሰሱም ተመላክቷል፡፡

በዚሁ መሰረት የአማራ ልዩ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ለጀግናው ልዩ ኃይል አባላትና መሪዎች እውቅና እየሰጠ መሆኑን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብሩ ለአባላቱና ለመሪዎቹ የማዕረግ እድገት እንደሚሰጥ እና በዚሁ መሰረትም ከረዳት ሳጅን እስከ ኮማንደርነት የማዕረግ እድገት ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከፍተኛ መኮንኖች፣ መሥመራዊ መኮንኖች በህልውና ዘመቻው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጀግኖች፣ የላቀ ግዳጅ ለፈፀሙ፣ የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የአማራ ልዩ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሚሊሻ እና ከፋኖ ጋር በመሆን ሕዝብን ደጀን አድርጎ አኩሪ ድል ማስመዘገቡም ተገልጿል፡፡