የሀገር ውስጥ ዜና

የመጀመሪያው የኢትዮ -ቻይና የጤናና የመድኃኒት ዘርፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ

By Meseret Awoke

May 31, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የኢትዮ -ቻይና የጤናና የመድኃኒት ዘርፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ።

በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከቤጂንግ ቤይ ማኦ ጂንግ ዩዋን ጤና አማካሪ ኩባንያ ጋር በጋራ በመተባበር በፋርማሴዩቲካል ዘርፍ ልማት ላይ ያተኮረ የንግድና ኢንቨስትመት ፎረም በበይነ መረብ ተካሂዷል።

በዚህም ከ45 በላይ በዘርፉ የተሰማሩ የቻይና ግዙፍ የፋርማሴዩቲካል ኩባንያዎችና ከ100 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፥ ፎረሙ ኢትዮጵያ ለፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልማት የሰጠችውን ቅድሚያና ልዩ ትኩረት ለቻይናውያን ኩባንያዎች ለማስተዋወቅና በኢትዮጵያ መዋዕል ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያሉ ሁለት ሶስተኛ ያህሉ የቻይና ኩባንያዎች በማኑፋክሪንግ ዘርፉ የተሰማሩ መሆናቸውን ተናግረው ፥ ይህም ኩባንያዎቹ በሀገሪቱ የገበያ አቅምና የኢንቨስትመንት አመቺ መዳረሻነት ያላቸውን ፅኑ እምነት የሚያመላክት መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም በዘርፉ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ መንግስት የቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክን ለዘርፉ አገልግሎት ብቻ ለይቶ ያዘጋጀ መሆኑንና የገበያ አማራጭ ዕድሎችንም ያመቻቸ መሆኑን አስረድተው፥ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት በማድረግ በሀገሪቱ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የእስያና ፓሲፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ ሁለቱ ሀገራት እ.ኤ.አ በ2017 ግንኙነታቸው ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ የትብብር አጋርነት ደረጃ ያሳደጉ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ቻይና የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልማት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ አቅራቢና ግንባር ቀደም የኢንቨስትመንት ምንጭ እንደሆነች የገለፁት ዳይሬክተር ጄኔራሉ ፥ የቻይና መንግስትና ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለሚያደርጉት አስተዋፅኦ መንግስት እንደሚያመሰግን ተናግረው ፥ በዘርፉ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

የቤጂንግ ቤይ ማኦ ጂንግ ዩዋን ጤና አማካሪ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሺ ሊሊ ፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት መቀመጫ መሆኗንና ያለችበት ጂኦግራፊያዊ መገኛ ለኢንቨስትመንት መዳረሻነት ተመራጭ እንደሚያደርጋትም ነው የተናገሩት።

የቻይና ኩባንያዎች በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በፎረሙ የጤና ሚኒስቴር፣ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያ ለፋርማሴዩቲካል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልማት ዙሪያ ማብራሪያዎችን ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።