አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል መንግስትና በክልሉ የሚገኙ የፌዴራል የጋራ ጸጥታ አካላት ኮሚቴ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የተለያዩ መመሪያዎች ሰጠ።
ውይይቱን የመሩት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ሲሆኑ ፥ በድንበር አካባቢ ሕገወጥ ንግድንና የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ እንቀስቃሴዎች በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በሰፊው ተወያይቷል።
በተጨማሪም የክልሉ ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ እና የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከፌዴራልና ከክልሉ ጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በዋጋ ንረትና ሕገወጥ የንግድ እንቀስቃሴ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንዲያደርጉ መመሪያ ተሰጥቷል።
በውይይቱ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልሉ ባለድርሻ ተቋማት መገኘታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።