አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጪውን ክረምት የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመቋቋም የሚሠራ ሀገር-አቀፍ ግብረ-ኃይል መቋቋሙን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
ግብረ-ኃይሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲቲዩትን ትንበያ መነሻ በማድረግ የጎርፍ አደጋ ሥጋት ካርታ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን የኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ግብረኃይሉ ከፌዴራልና ከክልሎች ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ሆኖ የጎርፍ አደጋ ሥጋቱን ለመቀነስና ለመቋቋም የሚያስችሉ ስራዎችን ያከናውናል ተብሏል።
ለተግባራዊነቱ የጎርፍ አደጋ ስጋት መለያ ካርታን ከማዘጋጀት በተጨማሪ የባለድርሻ አካላትን ሚና በመለየትና በመከፋፈል ወደ ሥራ መገባቱንም ነው የተናገሩት።
ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ በሚጠበቀው የጎርፍ አደጋ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስም የማስጠንቀቂያ መልዕክት የሚደርሳቸው በሥጋት አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ በማድረግ ለሥራው ተባባሪ መሆን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ባለድርሻ አካላትም ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በትዕግስት ስለሺ