የሀገር ውስጥ ዜና

ለዋግ ኽምራ ተፈናቃዮች ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት  ድጋፍ ተደረገ

By Shambel Mihret

June 06, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ ለተፈናቃዮች አድርጓል።

ድጋፉን ያስረከቡት የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ እንደገለጹት፥ ሃገረ ስብከቱ በሃገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎችን እያቀረበ ነው።

በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር እስካሁን ድረስ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በተደረገው ጥሪ መሰረት በውጭና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የወገን አለኝታነታቸውን አሳይተዋል ተብሏል፡፡

ከ7 ሚሊየን 400 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 3 ሺህ 421 ብርድ ልብሶች፣ 1 ሺህ 862 ፍራሾች እና 800 ኩንታል ዱቄት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ መደረጉንም አቡነ በርናባስ ገልጸዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ  ምላሽ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ÷ ሃገረ ስብከቱ ያደረገው ድጋፍ የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር የሚያቃልል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ከ89 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን÷ በጎ ፈቃደኛ ተቋማትና ግለሰቦች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-