ዓለምአቀፋዊ ዜና

ተመድ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት የምግብ ዕጥረት እና ረሃብ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቀ

By Alemayehu Geremew

June 09, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት ዕጥረት እና የረሃብ አደጋ በሀገራት ላይ ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አስጠነቀቁ፡፡

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሁለቱ ሀገራት ግጭት ተፅዕኖ ከግጭትነት ባለፈ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንደሚያስከትል በትናንትናው በዩክሬን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፉ የአደጋ ምላሽ ሰጪ ቡድን ሁለተኛ ዙር ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ሪፖርቱ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ዓለም አቀፉን የምግብ ፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓት እንደሚያናጋም አመላክቷል፡፡

በሀገራቱ መካከል የሚካሄደው ጦርነትም የማያባራ ከሆነ የሚያስከትለው ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት ሥር እየሰደደ እንደሚሄድ ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡

የሀገራቱ ግጭት በዓለማችን የተከሰቱት የዓየር ንብረት ለውጥ እና የኮቪድ19 ወረርሽኝ እያደረሱ ያሉት ተፅዕኖ እንዲባባስ ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት የምግብ በተለይም የበቆሎና የስንዴ እህል አቅርቦት እጥረት እንደተከሰተና የአፈር ማዳበሪያ ዋጋም ከእጥፍ በላይ እንደጨመረ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናግረዋል፡፡

በ94 ሀገራት የሚኖሩ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ሰዎች የተጠቀሱት አደጋዎች ገፈት ቀማሽ ሊሆኑ እንደሚችልም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ካለፈው ዓመት ምርት የተሰበሰበ 20 ሚሊየን ቶን ጥራጥሬ በዩክሬን እህል መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ እንደሚገኝም ነው የተነገረው።

ይህ ምርት በወጪ ንግድ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቢቀርብ የረሃብ አደጋ ስጋት ለቀንስ እንደሚችልና ገበያውንም እጅግ የማረጋጋት አቅም እንዳለው ፕረስ ቲቪ ዘግቧል፡፡