አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በ18 ወራት ውስጥ በዘመናዊ መንገድ ተገንብቶ በፍጥነት የተጠናቀቀውንና የፊታችን እሁድ የሚመረቀውን የገርጂ መኖሪያ መንደርን ጎበኙ፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ፣ የብሔራዊ መረጃና ድህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአርቲፊሻል ኤንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ጋቼና ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እና ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ናቸው ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሩን የጎበኙት፡፡
ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀውንና የፊታችን እሁድ በሚመረቀው በቀበና ሳይት ነው ከፍተኛ አመራሮቹ ጉብኝት ያደረጉት።
በጉብኝታቸውም በ18 ወራት ውስጥ እንዲዚህ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክት ማጠናቀቅ መቻል ኮርፖሬሽኑ ብቃት ያለው የፕሮጀክት መሪ እንዳለው የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በግንባታው ኢንዱስትሪ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የራሱን ደማቅ አሻራ ማኖሩን ገልጸው፥ የኮርፖሬሽኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚና መላውን የኮርፖሬሽኑን አመራርና ሠራተኛ ላስመዘገቡት የላቀ ውጤት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ አኗኗር ጭምር እያስተማረ ነው ያሉት ጎብኝዎቹ ፥ ያጋጠማችሁን ተግዳሮት ሁሉ በከፍተኛ እልህና አገራዊ ፍቅር ተቋቁማችሁ ፋይዳው ትልቅ የሆነ አገራዊ ፕሮጀክት እውን በማድረጋችሁ በኮርፖሬሽኑ ትልቅ ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል የፕሮጀክቱን ማሳካት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ፥ ተቋሙ ወደ ግንባታ ከመግባቱ በፊት ከአደራጃጀት ጀምሮ ያሉትን ክፍተቶች በጥናት በመለየትና ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመስራት ወደ ሳይት ትግበራ መገባቱን አሳተውሰዋል፡፡
እንደ አገር በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የራሳችንን አሻራ ማሳረፍ አለብን ብለን፤ በእልህ ተግተን በመስራታችን በ18 ወራት ይህን ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር እውን የማድረግ አቅም መፍጠር ችለናል ነው ያሉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!