አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ኤር ኤክስፕረስ አፍሪካ የግል የአውሮፕላን አየር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ሆኖ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ተመዘገበ፡፡
ተቋሙ ምዝገባውን በስኬት ያጠናቀቀው አለም አቀፍ አሰራርን ተከትሎ የተቀመጠውንና በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንም የሚተገበሩትን አምስት ደረጃዎችን በስኬት አጠናቆ በመገኘቱ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኤር ኤክስፕረስ አፍሪካ በዛሬው ዕለት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር የተፈረመበትን ሰርትፊኬት በይፋ ተቀብሏል፡፡
በዛሬው ዕለትበኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በተካሄደው የሰርቲፊኬት ርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ÷ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ተግዳሮቶች ያሉበት መሆኑን ተረድታችሁ ተስፋ ሳትቆርጡ በትጋት በመስራት ለስኬት እንድትበቁ እመኛለሁ ብለዋል፡፡
የኤር ኤክስፕረስ አፍሪካ መስራችና ባለቤት ካፒቴይን ነስሩ ከማል በበኩላቸው÷ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ኢንስፔክተሮች ሳይሰለቹ በመስራት ለዚህ ውጤት ስላበቁት ምስጋናየ ይድረሳቸው ብለዋል፡፡
ካፒቴይን ነስሩ ከማል ለረዥም አመታት በአውሮፕላን አብራሪነት ሙያ ላይ ተሰማርተው ሲያገለግሉ የነበሩ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በአሁን ሰዓት ኤር ኤክስፕረስ አፍሪካን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የአውሮፕላን አየር ትራንስፖርት ተቋማት 12መድረሳቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡