የሀገር ውስጥ ዜና

በሶማሌ ክልል በተያዘው ክረምት ከ847 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው

By Feven Bishaw

June 13, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመቀነስ በተያዘው የክረምት ከ847 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ያለውን የውሃ ሃብት አሟጦ በመጠቀም የፍራፍሬ እና የጓሮ አትክልት ልማት ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በተያዘው የክረምት ወቅትም ከፍተኛ የሰብል ምርት ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል።

በክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተሩ አቶ ባዳል ኪነዲን መሀመድ፥ ክልሉን በተደጋጋሚ እያጠቃ የሚገኘውን የድርቅ አደጋ ለመቀነስ የተደራጀ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

ለዚህም በተያዘው የክረምት ወቅት ከ847 ሺህ በላይ ሄክታር መሬትን በማልማት ክልሉን በተደጋጋሚ እያጠቃ ለሚገኘው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ከተዘጋጀው መሬትም 20 ሚሊየን 853 ሺህ 874 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ካለው ስራ ጎን ለጎን በ4 ሺህ 350 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ ለማልማት እንደታሰበ ኢዜአ ዘግቧል።

ከ21 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የቁም እንስሳት ክትባት በመስጠት ከጎረቤት ሀገራት ሊመጣ የሚችልን የእንስሳት በሽታ ለመከላከል እንደሚሰራም አስረድተዋል።

ዕቅዱን ለማሳካትም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ከፍተኛና ቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ባለፉት ሁለት ዓመታት በድርቅ ሳቢያ እየተፈተነ ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እንደሚደረግም ተገልጿል።