አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ በመንግስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚሰሩ ሴት መምህራን የተለያዩ ስጦታዎችን አበረከተ።
ኢትዮ ቴሌኮም “ትውልድ በመቅረጽ እና በማነጽ ጉልህ ሚና ያላቸው ሴት መምህራንን በማገዝ የሃገራችንን ብልጽግና እውን እናድርግ” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን በዛሬው ዕለት አክብሯል።
በበዓሉ ላይ ተቋሙ በመላ ሀገሪቱ በመንግስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ 20 ሺህ 477 ሴት መምህራን የተለያዩ ስጦታዎችን አቅርቧል።
ስጦታዎቹ 1 ጊጋ ባይት ነፃ ኢንተርኔት፣ 200 ደቂቃ ነፃ የድምጽ ጥሪ እና 200 ነፃ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች መሆናቸውን አስታውቋል።
ስጦታዎቹ ከየካቲት 29 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የሚበረከት መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የላቀ አፈፃፀም ካስመዘገቡ ምስጉን ሴት መምህራን መካከል እድለኛ ለሚሆኑ መምህራን 200 ስማርት ስልክ እና 50 ላፕቶፕ ኮምፒውተር በስጦታ እንደሚያበረክትም ነው የገለጸው።