ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሜክሲኮ ምዕራባውያን በዩክሬን ጉዳይ ላይ የሚከተሉትን ፖሊሲ አወገዘች

By Amele Demsew

June 15, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር መሳሪያዎችን ወደ ህይወት ገባሪ የጦር ቀጠና መላክ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ነው ሲሉ የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶር ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ምዕራባውያን ሀገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን የጦር መሳሪያ ድጋፍም አውግዘዋል፡፡

የሩሲያ- ዩክሬን ግጭትን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉት የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ግጭቱን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የለውም ብለዋል።

በአሜሪካ እና በአብዛኛዎቹ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አጋሮች በፖሊሲ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ለኬቭ የጦር መሳሪያ እርዳታ የማድረግ አካሄድ ግጭቱ የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ውድመት ያባብሰዋል ነው ያሉት፡፡

“ለጦርነት የሚውል በርካታ ገንዘብ መላክ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል? በርካታ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሲደረግ በርካታ የሰው ህይወት እንደሚጠፋ እንዴት መረዳት አልተቻለም?” ሲሉም ጠይቀዋል።

ምዕራባውያን ሀገራት ለጦርነቱ መባባስ ተጠያቂ እንደሆኑ እና ድርጊቱ ከስነምግባር ያፈነገጠ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል ፡፡

ጦርነቱን ማስቆም የሚቻልባቸውን መንገዶች ማፈላለግ ሲገባ ጦርነቱን በማባባስ የብዙ ሰው ህይወት እንዲጠፋ ማድረጉ የምዕራባውያን ፖሊሲን ውድቀት አመላካች ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የምዕራባውያን ፖሊሲ ከአሁን በኋላ መቀጠል የለበትም ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፖሊሲው የህዝብን ፍላጎት ያገናዘበ ሳይሆን በመሪዎች ብቻ የሚቀነቀን ነው ይህም ተገቢነት የለውም ማለታቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

የሩሲያን ኢኮኖሚ ለመጉዳት ያለመውን የምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ የምትቃወመው ሜክሲኮ ለዩክሬን የሚደረገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ አካሄድ እንደማትደግፍም አቋም ይዛለች ነው የተባለው፡፡