ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኬንያ ከኮቪድ19 ሥርጭት ዳግም መቀስቀስ ጋር ተያይዞ ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲጠቀሙ በድጋሚ አወጀች

By Alemayehu Geremew

June 21, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬንያ ቀንሶ የነበረው የኮቪድ19 ሥርጭት ዳግም መቀስቀሱን እና የሀገሪቷ ጠቅላላ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ ዜጎቿ ማስክ መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ በድጋሚ አወጀች፡፡

የኬንያ ጤና ሚኒስትር ሙታሂ ካግዌ ÷ ዜጎች በማናቸውም ቦታዎች ማስክ የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ሰኞ ዕለት 1 ሺህ 993 ኬንያውያን የኮቪድ -19 ምርመራ አድርገው 252 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ጤና ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቷ ጤና ሚኒስቴር ካሳለፍነው የፈረንጆቹ መጋቢት ወር ጀምሮ አስገዳጅ የነበረውን ማስክ የመጠቀም አዋጅ አንስቶ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የኅብረተሰብ ጤና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ፍራንሲስ ኩሪያ ገልጸዋል፡፡

በሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ተመራማሪዎች 6ኛው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሀገሪቷ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡

እስከ ትናንትና ድረስ በኬንያ የኮቪድ-19 ክትባት ሙሉ ለሙሉ ወስደው ያጠናቀቁ ዜጎች ቁጥር በመቶኛ 31 ነጥብ 5 የደረሰ ሲሆን መንግስት ዓመቱ ከመገባደዱ በፊት 70 በመቶ ለማድረስ ዘመቻ መጀመሩን የሀገሪቷ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጿል።

የፊታችን ነሐሴ 9 ኬንያ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ታካሂዳለች።