የሀገር ውስጥ ዜና

ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ከትናንት ጀምሮ መውሰድ በጀመረው ኦፕሬሽን ጠንካራ አስተማሪ ስራ እየሰራ ነው-ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

By Meseret Awoke

June 21, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ከትናንት ጀምሮ መውሰድ በጀመረው ኦፕሬሽን ጠንካራ የማስተማሪያ ስራ እየሰራ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አራተኛውን ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ የእጽዋት ማዕከል አስጀምረዋል፡፡

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለመጓዝ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ሶስት ነገሮችን በአንክሮ መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት ፡፡

እነሱም “ኢትዮጵያ እና ኢትጵያውያን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለባቸው፤ ሃብት በማሰባሰብ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከተፈጥሮ ጋር ታርቀን ያሉብንን ችግሮች መቅረፍ ይኖርብናል” ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ እና ኢትጵያውያን እምቅ ሃብቶቻችንን መጠቀም መጀመር አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም “ከኢትጵያውያን የሚጠበቀው ሃገራችንን መንከባከብ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ መንከባከብ ሲባል ሃገር ምድር ብቻም ሳይሆን ሰውንም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ ከወታደር እና ከፖሊስ ጋር በቀጥታ መግጠም የማይችሉ ተላላኪ ባንዳዎች ንፁሃን ኢትዮጵውያንን ይጨፈጭፋሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር፥ ይህን ማስቆም ከሁሉም እንደሚጠበቅ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን መኖር የማይችሉበት ምድር ለማድረግ እና የያዝናቸውን መልካም ሃሳቦች ለማጨናገፍ የሚሞክሩ ሃይሎችና ተላላኪዎቻቸው ትልሞቻቸው እንዳይሳካም መከፋፈል ሳይሆን ሰብሰብ ብለን በተደመረ ክንድ ጠላቶቻችንን ማሳፈር ነው ብለዋል፡፡

ዜጎቻችንን የጨፈጨፉትንም በህግ አግባብ ማስተማር ይጠበቅብናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ጀግናው የመከላከያ ሚኒስቴር ከትናንት ጀምሮ መውሰድ በጀመረው ኦፕሬሽን ጠንካራ የማስተማሪያ ስራ እየሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሆኖም የሁሉንም አመራር ትኩረት ይሻል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በቀኝ እጃችን ልማታችንን እናስቀጥላለን በግራ እጃችን ደግሞ ጠላቶቻችንን እንዋጋለን፣የሚቆም ነገር የለም ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!