አዲስ አበባ፣የካቲት 29፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሰሜናዊ ጣሊያን 16 ሚሊየን ሰዎች በልየታ(በኳራንቲን) እንዲቀመጡ መደረጉ ተገለጸ፡፡
ጣሊያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ በሽታውን ለመቆጣጠርና ስርጭቱን ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡
ለዚህም በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል 16 ሚሊየን ሰዎችን በ14 አውራጃዎች እስከ ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ድረስ ተለይተው እንዲቀመጡ ማድረጓ ተገልጿል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ከአደጋ ጊዜ በስተቀር መውጣትም ሆነ መግባት እንደማይቻል ነው የተገለጸው፡፡
ከዚህ ባለፈም የስፖርት ቤቶች ፣ የመዋኛ ገንዳዎች ፣ ሙዚየሞች እና የበረዶ ላይ መዝናኛዎች ይዘጋሉ ነው የተባለው፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ÷ እንደዚህ አይነት እርምጃዎች አንዳንድ ጊዜ ትናንሽ እና አንዳንዴ ደግሞ ትልቅ መስዕዋትነትን ሊያስከፍሉ ይችላሉ ብለዋል፡፡
አያይዘውም ጊዜው ሁላችንም ለራሳችን ሃላፊነት መውሰድ ያለብን ወቅር ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የሃገሪቱ መንግስት የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሚል ትምህርት ቤቶችን እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መዝጋቱ ይታወሳል።
በአሁን ሰዓት በጣሊያን በቫይረሱ ምክንያት ከ230 በላይ ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን ÷ ከ5 ሺህ 888 በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ምንጭ፡-ቢ.ቢ.ሲ