አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ሴቶች በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ የሚበረታታና ቀጣይ ውጤቶችም የሚመዘገቡበት መሆኑን ገለጹ።
ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ በሴቶች ብቻ የሚመራ የበረራ ቡድን ትላንት ማምሻውን ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ማቅናቱ ታውቋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የሴቶች ጉዳይ በዓመት አንድ ቀን ብቻ ታስቦ የሚቀር ሳይሆን በየቀኑ ሊሰራበት የሚገባ ነው ብለዋል ።
በአገሪቷ አሁን እየታዩ ያሉ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚበረታታና ወደ ፊትም በርካታ ውጤቶች ሊመዘገቡበት እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን የተያያዘችውን የለውጥ ጎዳና ለማሳደግ ሴቶችን በተለያዩ መስኮች ተሳታፊ ማድረግና በትምህርት ማብቃት ቁልፍ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ሴቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቷ አያይዘውም የሴቶች ጉዳይ ለሴቶች ብቻ የሚተው ባለመሆኑ በማሕበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስክ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በበኩላቸው÷ አየር መንገዱ ሴቶችን በማብቃት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ መሆኑን አንስተዋል።
በተቋሙ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 32 በመቶ በሃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰሩት ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመው÷ ሴቶች የተለየ እገዛ የሚፈልጉ ሳይሆን የተሰጣቸውን ሃላፊነት የሚወጡ ለመሆናቸው በርካታ ማሳያዎች መኖራቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡