የሀገር ውስጥ ዜና

ለውጡን ተከትሎ በፖለቲካው መስክ የተጀመሩ አካታች አካሄዶች ዜጎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰለፉ እድል የፈጠሩ ናቸው-የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት

By Mikias Ayele

June 24, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፖለቲካው መስክ የተጀመሩ አካታች አካሄዶች ዜጎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰለፉ እድል የፈጠሩ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት እንደገለጹት÷ ባለፉት አራት ዓመታት በተለይ በፖለቲካው መስክ አሳታፊ ምህዳር ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት እንደ አገር በርካታ እድሎችን የፈጠሩ ናቸው፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሙፈሪያት ካሚል÷አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፓለቲካ አዲስ ምእራፍ የከፈቱ አካሄዶች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ስር ሰዶ የቆየውን የመጠላለፍና የመጠፋፋት የፖለቲካ አካሄድ እንዲቀየር ከማድረጉ በላይ ገዥና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ አገር እንዲመሩ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ለውጡን የሚመራው መንግስት የቆዩ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱንም ነው የተናገሩት፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊና የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው÷ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና የኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለጫ የነበረውን የጠላትና ወዳጅ አካሄድ በአጭር ጊዜ ወደ አካታች ምህዳር መቀየር መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የሽግግር ሂደት ጊዜን የሚጠይቅና በፈተና የሚያልፍ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስፈጻሚዎቹ÷ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ስኬቶች ቢመዘገቡም አገርን የፈተኑ አደጋዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በተለይ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ የተፈጠረውን ነጻነት በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ በህዝብና አገር ላይ አደጋ የሚፈጥሩ አካላት እየተበራከቱ እንደመጡ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኀብረተሰቡ የህግ የበላይነት እንዲከበር በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱን የገለፁት ስራ አስፈፃሚው ÷ መንግስት ወቅታዊ አገራዊ ፈተናዎችን በመገምገም የአገርና ህዝብ ድህንነትን ለማስጠበቅ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት እያከናወነ ለሚገኘው ህግ የማስከበር ስራ ኀብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው÷ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡንም ተናግረዋል፡፡