የሀገር ውስጥ ዜና

የግብርና ምርምር ማዕከሉ 58 ዓይነት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ተደራሽ አድርጓል

By Shambel Mihret

June 28, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቢሾፍቱ የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል 58 ዓይነት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ምርታማነት በእጥፍ እንዲጨምር ማስቻሉን ገለጸ፡፡

በግብርና ምርምር ማዕከሉ የብሔራዊ የጤፍ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ወርቁ ከበደ÷ በተያዘው ዓመትም ሁለት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰው፤ የጤፍ ምርታማነት እንዲጨምር የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።

ዘሩን በማዳቀል እና በቤተ-ሙከራ የሚፈለገው ንጥረ ነገር እንዲኖሩት በኬሚካል በማድረቅ የዘር ማሻሻያ ምርምር እየተሰራ ስለመሆኑም አስተባባሪው ተናግረዋል።

በማዕከሉ የሚወጡ የምርምር ውጤቶች በቂ ዝናብ ለሚያገኙ፣ ዝናብ አጠር ለሆኑ እንዲሁም ለደጋ አካባቢዎች የሚስማሙ የጤፍ ዝርያዎችን ማቅረብ መቻሉን አስረድተው የዝናብ እጥረት ለሌለባቸው አካባቢዎች ብቻ የሚስማሙ 38 የጤፍ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች መሰራጨታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተሰራው የምርምር ሥራ የጤፍ ምርታማነት መጨመሩን ጠቅሰው፤ በዚህም በ1 ሄክታር መሬት 8 ኩንታል ይገኝ የነበረውን ምርት ከ18 እስከ 20 ኩንታል ከፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የጤፍ ዝርያን ዘርተው በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚያደርጉ የግል እና የመንግሥት ድርጅቶችም ከ1 ሄክታር ከ25 እስከ 30 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገር ደረጃ የጤፍ ምርት የሚዘራበት የማሳ ስፋት ድሮ ከነበረው 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ወደ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል፡፡

በአገር ደረጃ በዓመት ይገኝ የነበረው ምርትም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ከፍ ብሎ በአሁኑ ወቅት ወደ ከ6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ መድረሱንም መጠቆሙን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!