የሀገር ውስጥ ዜና

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ ተገለጸ

By Meseret Awoke

June 29, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ የትምህርተ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሆሳዕና ፣ በወራቤና በወልቂጤ ከተሞች የሚገኙ ሁለተኛ ደረጃና ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው ወቅትም ከተማሪዎችና ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በትምህርት ቤቶች ሳይሆን በዩኒቨርስቲ ውስጥ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ፥የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በኦንላይን መስጠት እስከሚጀመር ድረስ በዩኒቨርስቲዎች መሰጠቱ ይቀጥላል።

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ የተወሰነው የፈተና ሰርቆትና ማጭበርበርን ለማስቀረት ታስቦ በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርት በስራና በታታሪነት የሚገኝ መሆኑን አውቀውበርትተው መማርና ማጥናት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትን ጥራትን ለማሻሻል በአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፎች ሌሎችንም የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑንም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ ሶስቱንም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጎበኙ ሲሆን÷ በዚህም ለአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ችግኝ መትከላቸውን ከሚኒሰቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!