አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገር አቀፍ ደረጃ በ400 ጤና ጣቢያዎች ላይ በተደራጀ መልኩ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አንስቴዥያ ባለሙያዎች ማህበር “የእናቶች እና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ጥራት ያለው አገልግሎት ማበርከት ያስፈልጋል” በሚል መሪ ሃሳብ 15ኛውን ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በጉባዔው መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ፥ በአገር አቀፍ ደረጃ ከወሊድ ጋር የተያያዘ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ከ3 እስከ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም አገልግሎቱን ሳያገኙ ለውስብስብ የጤና እከል የሚዳረጉና የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በተለይ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እንደ አገር የቀዶ ህክምና አገልግሎትን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።
ሚኒስቴሩ ከማህበሩ ጋር በመቀናጀት የሕክምና ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ በ400 ጤና ጣቢያዎች ራሱን የቻለ የቀዶ ሕክምና መስጫ ህንጻ በመገንባት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበው፤ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ነው የረጋገጡት ፡፡
የኢትዮጵያ አንስቴዥያ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ልዑልዓየሁ አካሉ ፥ ማህበሩ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች አስፈላጊውን እውቀት ይዘው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ የማብቃት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከፍተኛ የሙያ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የአንስቴቲስቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ከ1 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን ፥ ጉባዐየውም በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ መሆኑን ከማህበሩ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!