የሀገር ውስጥ ዜና

በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተገለጸ

By Alemayehu Geremew

July 18, 2022

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈጠራ ሥራ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

ዶክተር ሊያ በአምስት አመቱ የጤና ስትራቴጂክ ዕቅድ ጥራት ያለው አገልግሎት በማጎልበት የተሻለ ጤና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ጥራትን ለማምጣት ደግሞ የፈጠራ ሥራዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው ነው ያሉት፡፡

በዚሁ መሠረት በዛሬው ዕለት “ግራንድ ቻሌንጅ ኢትዮጵያ” ከ “አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት” በተደረገለት ድጋፍ የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

ከሰባት ዓመት በፊት ወደ ሥራ የገባው “ግራንድ ቻሌንጅ ኢትዮጵያ” ለተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

“አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት” ÷ እስካሁን 550 የፈጠራ ሥራ ፕሮፖዛሎች ቀርበውለት ለ70ዎቹ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ነው የተባለው፡፡

አሁን ላይ አራት የፈጠራ ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ገበያ ሊወጡም እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በጤናው ዘርፍ እየተሠሩ ከሚገኙ የፈጠራ ሥራዎች መካካል 67 በመቶዎቹ የእናቶችና ሕጻናትን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዱ ናቸው ብለዋል።

ከአጠቃላይ በጤና ዘርፍ ከተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች መካካል 60 ከመቶው በጅማ ዩኒቨርሲቲ መሠራቱን ዶክተር ሊያ ገልጸው ለዩኒቨርሲቲው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በጤናው ዘርፍ ”አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት” ለ”ግራንድ ቻሌንጅ ኢትዮጵያ” የፈጠራ ሥራዎች 2 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በተመስገን አለባቸው